Skip to main content

The Booksellers on the Street

Mohammed Selman is a journalist and freelance writer, presently working for BBC Amharic. He previously edited at Littmann Books, a leading publishing house in Ethiopia, as reporter and columnist for Addis Neger, a weekly newspaper closed long time ago. In “The Booksellers on the Street,” his readers can glimpse how authors, publishers and street vendors warily united to deliver books in Ethiopia’s capital, Addis Ababa. There, under continuous government fire, the explosive power of books kept freedom of expression alive for readers.

Credits Text: Mohammed Selman May 03 2019

አቶ ኃይለማርያም የሚጠጣ ምን ይምጣ ሲባሉ ‹‹መለስ የጀመረው ቀዝቃዛ ቢራ…›› በሚሉበት ዘመን አንድ ማለዳ…

በአርታኢነት ወደምሠራበት መጽሐፍ ቤት ስገባ ይህን ተመለከትኩ፡፡ እስካፍንጫቸው መሣሪያ የታጠቁ ፌዴራሎች ከሼልፍ ላይ መጽሐፍ እየመረጡ…፡፡ ታዲያ ኢየሱስ መምጫው አልደረሰምን…?

ያን ሰሞን ኢህአዴግ ‹‹ሙዱ ተከንቶ›› ስለነበር በራሪ አእዋፋትን ሳይቀር ያስር ነበር፡፡ እኔንም በቁጥጥር ሥር ሊያውሉኙ የመጡ መስሎኝ ራድኩኝ፡፡ የመደብራችንን ካሸር ወደ ረዥሙ ሼልፍ ጎተት አድርጌ ‹‹አለቀልን?›› አልኳት፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካን የሚገልጥ ቁና እየተነፈስኩ፡፡ ፈገግ ብላ "ኸረ ለፌዴራል ፖሊስ ላይብረሪ የሚሆን ጨረታ አሸንፈን ነው" አለችኝ፡፡

ለካንስ ፌዴራሎቹ ከነጦር መሣሪያቸው የመጡት እኔን ለመማረክ ሳይሆን መጻሕፍቱን ለመረከብ ነበር፡፡

ብቻ መጻሕፍት ከሼልፍ እየወረደ፣ በየፈርጁ እየተቀነበበ ወደ ካርቶን እየተሞጀረ በሲባጎ ይጠፈራል፡፡ ልክ ፌዴራል ‹‹ጸረ ሰላም ኃይሎችን›› ይዞ የፊጢኝ እንደሚያስራቸው ዓይነት፡፡

አንዱ ካርቶን ሊታሸግ ሲል ግን ዐይኔ ማየት የሌለበትን አየ፡፡ ‹‹የመለስ አምልኮ›› የሚል መጽሐፍ፡፡ ተገረምኩ፡፡ አንደኛ ይህ መጽሐፍ አዝዋሪዎች ራሳቸው ፈራ ተባ እያሉ የሚሸጡት ዓይነት ነበር፡፡ ሁለተኛ ፌዴራል ፖሊስ በምንም ተአምር ይህንን መጽሐፍ ሊገዛ አይችልም፡፡ ምናልባት እኔ ያልሰማሁት በተመስገን ደሳለኝ የተመራ ልዝብ መፈንቅለ መንግስት ካልተካሄደ በስተቀር…ይህን መጽሐፍ ፌዴራል ሊገዛው አይችልም፤ በፍጹም፡፡

የመጣው ይምጣ ብዬ ከአንደኛው ባለማዕረግ ፌዴራል ጋ ጨዋታ ጀመርኩ፡፡

‹‹…ሕዝቡ ዝም ብሎ ይፈራችኋል እንጂኮ ለኛው ደህንነት ነውኮ እናንተም የቆማችሁት…፡፡›› ደረቅ ፌዴራላዊ ፈፈግታ አሳየኝ፡፡

‹‹…ግን ገርሞኛል ይህን መጽሐፍ መግዛታችሁ…›› በጣቴ ወደ መጽሐፉ እየጠቆምኩ ተንተባተብኩ፡፡ መጠነኛ ሲቪላዊ ፈገግታ አሳየኝ፡፡ የምለው እንዳልገባው ገባኝ፡፡ መጽሐፉ አቶ መለስን ከፍ ዝቅ የሚያደርግ እንጂ ከፍ ከፍ የሚያደርግ እንዳልሆነ ጭራሽ አልጠረጠረም፡፡

‹ይቅርታ…ርእሱ አሳስቷችሁ እንዳይሆን ብዬ ነው፣ …ደራሲው ራሱ ዝዋይ ነው…››

ለካስ ፌዴራልም ይደነግጣል፡፡ ከታላቁ ኅዳሴ ግድብ የሚመነጭ ኤሌክትሪክ የነዘረው ነው የመሰለው፡፡ አለቃውን ጠርቶ ነገረው፡፡ አለቃው በእጥፍ ደነገጠና የአለቃውን አለቃ ጠርቶ ነገረው፡፡ ትልቁ አለቃ በትልቁ ደነገጠና ስልኩን አወጣ፡፡ ስልክ አወጣጡ ከኮልት አወጣጥ ጋ ይመሳሰል ነበር፡፡ ከመደብራችን ወጣ ብለው ተነጋገሩ፤ አንዳንድ ቦታም ደዋወሉ፡፡ ሲመስለኝ ወደ ሜክሲኮ ነው የደወሉት፡፡

ብዙ እዚህ የማይጻፍ ነገር ከሆነ በኋላ የአለቃቸው አለቃ ወደኔ ጠጋ ብሎ፣ "እኛ ስለ ታላቁ መሪ የተጻፉ ካሉ በርከት አርጋች ግዙ ተብለን ነው፤ አላወቅንም አቦ፤ እግዛቤር ይስጥህ! ከብዙ ችግር ነው ያወጣኸን" አለኝ፡፡

የመጽሐፍ ርእስ እንዴት አንድ ሙሉ የግዢ ኮሚቴን ይሸውዳል፡፡ መጽሐፍን ገልጦ ያለማንበብ ችግር…አልኩ በልቤ

ፌዴራል ብቻ ሳይሆን እነ ኃይልሻም ሕዝቡን የማንበብ ችግር ነበረባቸው፡፡

ብቻ በዛች አንድ መጽሐፍ ምክንያት የስንትና ስንት ሺ ብር ጨረታ ግዢ ተሰረዘ እላችኋለሁ፡፡

ያን ለታ ፌዴራሉ ደግሞ ደጋግሞ አመሰገነኝ፤ ባለመጽሐፍ ቤቱ ቀጣሪዬ ግን ሙሉ ቀን አኮረፈኝ፡፡

ኾኖም በነገታው አስጠራኛና‹‹መሐመድ! ሳስበው ትናንት ጥሩ ነው ያረከው፤ እንኳንም ቀረብን፣ ለኛ ያለው ሪዝቅየትም አይሄድም፡፡ ባለቤቴን ስነግራት እኮ…ይሄ የአላህ ተአምር ነው አለችኝ፡፡ ገዝተውት ቢሆን ዳፋው ለኛም ይተርፍ ነበር አለችኝ፡፡››

"የመጽሐፍ-በደረቴዎች" ደረት
ህወሓት የአቶ ኃይለማርያምን ሰፊ ትከሻና ደረት ከፊት አጋልጦ አገሪቱን ከጀርባ በሚዘውርበት በዚያ ዘመን መጽሐፍ በደረቴዎች አልፎ አልፎም ቢሆን ይንገላቱ ነበር፡፡ ለምሳሌ ‹‹የመለስ ልቃቂት›› የሚል መጽሐፍ ይዘው ከተገኙ የኤልቻፖ ኮኬይን የተገኘባቸው ያህል መቀጣጫ ይደረጉ ነበር፡፡ ኋላ ላይ መላ ዘየዱ፡፡ መጻሕፍትን በሁለት ከፈሏቸው፡፡ የደረትና የጀርባ በሚል፡፡

እንደ ፈረንጅ ልጅ በደረት የሚታዘሉት ከመንግሥት ጋ ፀብ ውስጥ የማያስገቡ፣ የቧልት፣ የፍቅር፣ የጤናና የልቦለድ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ፣ እንደ ገጠር ልጅ በጀርባ የሚታዘሉት ደግሞ በግላጭ ቢታዩ ለአደጋ የሚያጋልጡ ‹‹መዘዛም›› መጻሕፍት ናቸው፡፡ ከመዘዛም መጻሕፍት መሀል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

ርዕዮት ‹‹የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ››፣ የተመስገን ‹‹የፈራ ይመለስ›› የብርሃኑ ‹‹የነጻነት ጎህ ሲቀድ››፣ የሲሳይ ‹‹የቃሊቲ መንግሥት››፣ የኤርሚያስ ‹‹ባለቤት አልባ ከተማ››፣ የተስፋዬ ‹‹የቡርቃ ዝምታ››፣ ታደለ ቱፋ ‹‹ማዶላ››፣ ይጠቀሳሉ›› የአንዳርጋቸው ጽጌ ‹‹ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች››፣ የፕ/ር ጌታቸው ‹‹የአባ ባሕሪ ድርሰቶች››፣ የፕ/ር መስፍን ‹‹አገቱኒ››፣ የሙሉቀን ተስፋው ‹‹የጥፋት ዘመን›› እና ‹‹የክፉ ሰው ሽንት››፣ የአንዳርጌ መስፍን ‹‹በሙት መንፈስ አገር ሲታመስ››፣ የሐብታሙ ስዩም ‹‹17 መድፌና ሃያ ምናምን ቁምጣ››፣ የሙሉጌታ ሉሌ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን››፣ የነገደ ጎበዜ ‹‹ሕገ መንግሥት፣ ምርጫና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ›› ወዘተ…፡፡ የእስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ፕ/ር መረራ፣ ውብሸት፣ ሰለሞን ከበደ፣ አሕመዲን ጀበል እና ሌሎች በርካታ ሰዎች መጽሐፎቻቸውን ወይ ለማተም ወይ ለማሰራጨት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ፈተና ነበር፡፡

ይህን ጽሑፍ የሚያነቡ በርካታ ሐቀኛ ሰዎች መጻሕፍቱን ያለ ችግር ጎዳና ላይ እንደ እንትን መንገድ ላይ ተሰጥተው ስለተመለከቷቸው፣ ያለችግር ከአዝዋሪ ገዝተው ስላነበቧቸው የማወራውን በጥርጣሬ እንደሚመለከቱ እጠረጥራለሁ፡፡ እነርሱ እጅ ከመድረሳቸው በፊት ግን መጽሐፍቱ ያዩትን ውጣ ውረድ የሚያውቁት አሳታሚና አከፋፋዮች ናቸው፡፡ ስለማወራው ነገር ይበልጥ ለመረዳት እባክዎ በአካባቢዎ የሚያዘግም መጽሐፍ በደረቴን ያነጋግሩ፡፡

በመጻሕፍቱ ቁጥጥር ዙርያ በመንግሥት ደረጃ ወጥ አቋም ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህን የምለው እጅግ የሚፈሩ መጻሕፍት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጨረታ ዝርዝር ውስጥ እመለከተት ስለነበር ነው፡፡ የአገር ደህንነት መሥሪያ ቤት ለቤተ መጻሕፍት ግዢ በጠየቀው ሰነድ ዝርዝር ውስጥ የፕሮፌሰርን መክሸፍ ማየቴን አልዘነጋም፡፡

ኢህአዴግ የውርድንብር ውስጥ ሲገባ አስቂኝ የጎረምሳ ባሕርያትን ይላበሳል፡፡ ለምሳሌ የፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹የአማራና የኦሮሞ የዘር ግንድ›› የሚለውን በይዘቱ ‹‹ህም›› የሆነን መጽሐፍ ሽጣችኋል ብሎ ስንት ልጆችን ገረፈ መሰላችሁ፡፡ ይሄ እንዲያውም አያስቅም፡፡ ‹‹ሳታወላውል አድርገው›› የሚል አንድ ስሜት-አጧዥ መጽሐፍ ነበር፡፡ ፖሊሶች የአመጻ ጥሪ መስሏቸው ብዙ አዝዋሪዎችን አንገላተውበታል፡፡

ስለ‹‹የተቆለፈበት ቁልፍ›› አልሰማችሁ ይሆናል ይህን ጊዜ፡፡ ከርእሱ ብቻ ተነስተው አንዳንድ ፖሊሶች ይህን መጽሐፍ ለአጭር ጊዜ ይቀሙ ነበር፡፡ ይህን የነገረኝ አዝዋሪ ‹‹ማን ላይ ነው የምትቆልፈው›› ተብሎ ስስ ጥፊ ቀምሷል፡፡ ዶ/ር ምሕረት ለዚህ አዝዋሪ ‹‹ጥፊን የመቋቋም መርህ እና ስልቶች›› የሚል አጭር ስልጠና በኮከብ ሆቴል ውስጥ ጠርቶ እንደሚሰጠው ተስፋ አድርገን እናዝግም››

***

ደራሲዎች ሕዝብን ነጻ ለማውጣት በጻፉት ይታሰራሉ፡፡ አዝዋሪዎች ይህን የነጻነት መልእክት ለሕዝብ አድርሶ ኑሮን ለመደጎም በሚሞክሩበት ጊዜ ይታሰራሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የመናገር ነጻነትን ለመለጎም የሚደረግ ጥልፍልፍ ነው፡፡ መንግሥት ወይ መልእክተኛውን ወይ መልእክት አድራሹን እያሠረ ነጻነትን ያፍናል፡፡

መልእክት አድራሾቹ ሲታሰሩ ዋስ ሆነው የሚያስፈቷቸው መልእክት አሳታሚዎች ወይም ያልታሠሩ የመልእክቱ ደራሲዎች የሚሆኑበት አጋጣሚም አለ፡፡ አንዳንድ አዝዋሪዎች ወደ አሳታሚና አከፋፋይነት አድገው አይቻቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ደራሲነት ሁሉ ይዳዳቸዋል፡፡ ከበዕውቀቱ ስዩም ጎዳና (ከአክሱም ሆቴል እስከ ቺቺኒያ) ከራሱ ከደራሲው ጋር ባዘገምኩበት አጋጣሚ መጽሐፍ አዝዋሪዎች እያስቆሙ ‹‹ይቺን ሙከራዬን እያትና እንደሚሆን አበጃጃት እስቲ›› ብለው የጫጫሩትን ሲሰጡት በአንድ ሁለት አጋጣሚ አስተውያለሁ፡፡

***

በደረቴዎች መዘዛም መጻሕፍትን ከጭምት መጻሕፍት ይልቅ አብልጠው ይወዳሉ፡፡ ዋንኛው ምክንያታቸው ጠቀም ያለ ትርፍ ስሚያስገኙላቸው ይመስለኛል፡፡ እነዚህን መዘዛም መጻሕፍት ለደንበኞቻቸው የሚያሻሸጡበት ዘዴ የአደገኛ ዕጽ ቅብብል ሰንሰለትን ይመስላል፡፡

መጀመርያ የደንበኛቸውን ፖለቲካዊ ዝማሜ ይገመግማሉ፡፡ ከያዝዋቸው መጻሕፍት የትኛውን እንደሚመርጥ ይመለከታሉ፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚ ይሁን ደጋፊ ለማወቅ ጫወታቸውን እንደ ክራር ቀድመው ይቃኙታል፤ ለምሳሌ ውይይታቸው ይህን ሊመስል ይችላል…

አዝዋሪ፡-ፀሐይዋ ዛሬ ደሞ እስከነልጆችዋ ነው የወጣችው፣ ምን ዓይነት መጽሐፍ ላሳይህ ወንድሜ…

ገዥ፡-ታቃጥላለች አይደል?

አዝዋሪ፡-ታቃጥላለች ብቻ! ወያኔን ሆነችብን እኮ…

(ደንበኛው በዚህ አባባል ካልተቆጣ የመንግሥት ሰው እንዳልሆነ ስለሚገመት ጠጠር ያሉ መጻሕፍት ከጀርባ ቦርሳ እየወጡለት እንዲጎበኛቸው ይደረጋል)

ሌላ ምሳሌ፡-

አዝዋሪ፡-ጋሼ ምን ዓይነት መጽሐፍ ላሳይዎ? የዳንኤል ክብረት አዲሱ አለኝ…

ገዥ፡-አይ አልፈልግም…

አዝዋሪ፡-የይስማእከም ‹‹የቀንድ አውጣ ኑሮ›› አለኝ፡፡ የኛ ኑሮ ራሱ ከቀንድ አውጣ ባይለይም…ህም!

ገዥ፡-እረ ተወኝ አንተ ልጅ፣ እኔ መጽሐፍ አልወድም…

አዝዋሪ፡-ጋሼ…እዚህ አካባቢ ቁጭ ሲሉ አይሸቶትም ግን፤ የሆነ ቱቦ ግም ግም ይሸታል….፡፡ ለነገሩ ይቺ ከተማ መች ባለቤት አላትና..

ህ! (ገዢ በመገረም ዐይኑን ሲያቁለጨልጭ)

አዝዋሪ፡- (ወደ ገዥ ጆሮ ጠጋ ብሎ)…ጋሼ የኤርሚያስ ለገሰን ‹‹ባለቤት አልባ ከተማ››ን አንብበውታል? ካላነበቡት ላምጣልዎ…ዋጋ አያጣላንም…

***

የመጻሕፍት አዝዋሪዎች ምላጭ
በአዲስ አበባ መጻሕፍ አዝዋሪዎች እንደ ብልት ገራዥ ምላጭ በሸሚዝ ኪሳቸው ይዘው ይዞራሉ፡፡ የዚህ ምላጭ አገልግሎት በየመጻሕፍቱ ጀርባ የሚቀመጠውን ዋጋ መፋቅ ነው፡፡ከምላጮ ጎን ጥቁር ብዕር ያኖራሉ፡፡ በዚህ ብዕር ደግሞ ለሚያዝሏቸው መጻሕፍት አዲስ ዋጋ ተምነው፣ አጽድቀው ያትሙበታል፡፡ አዲሱ የዋጋ ተመን ታዲያ አዝዋሪዎቹ የሚዞሩበትን ሰፈር፣ የዕለቱን የፀሐይ ኃያልነት፣ የመጽሐፉን ድልብነት፣ የይዘቱን መርዛማነት፣ እንዲሁም የደራሲውን ዝናና የእስር ዘመን ከግምት ያስገባ ነው፡፡ ኦፔክራሱ የነዳጅ ዋጋን ሲከልስ በዚህ ዝርዝር ነገሮችን የሚያጤን አይመስለኝም፡፡

አዝዋሪዎች ለመጽሐፍ አዲስ ተመን ሲያወጡ ቦሌ መድኃኒዓለምና አካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ የዋጋ ብዝበዛ ይጋለጣሉ፡፡ በሁለት ምክንያት፤ አንደኛ ቦሌዎች ዋጋ የቱንም ያህል ቢቆለልባቸው እምብዛምም አይሰማቸውም ተብሎ ስለሚገመት፡፡ ሁለተኛ እዚያ ሰፈር መጻሕፍቱን የሚገዙት ልክ ባለጸጎች ውድ ሥዕል እንደሚገዙት ዓይነት ለሥነውበት ዕሴቱ (Aesthetic value) እንጂ ለይዘቱ አይደለም ተብሎ በደፈናው ስለሚታመን፡፡

***

ሰው ስስ ፌስታል ለመግዛት ሸዋ ሱፐርማርኬት እንደማይሄደው መጽሐፍ ለመግዛት መደብር አይሄድም፡፡ በዘመን መገለባበጥና መዳፈ-ስልክ ባንሰራፋው ስንፍና የተነሳ መጻሕፍት ተራራ ሆነዋል፡፡ ሕዝብ ወደ ተራራው አይሄድም፤ ተራራው ወደ ሕዝብ መምጣት አለበት፡፡ ልክ ሕዝብ ማንበብ ሊያቆም ሲል ይህን ተራራ በደረታቸው ተሸክመው የሚዞሩ ብሩክ ልጆች ተፈጠሩ፡፡

ብዙ ሰው ንባብን ያስፋፉት ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ይመስሉታል፡፡ ንባብን ያስፋፉት መጽሐፍ አዝዋሪዎች ናቸው፡፡ ይህን የምለው ከጃፓኖችም ከፍ ባለ እርግጠኝነት ነው፡፡ የኛ ሰው አሳንሱር ከመሳፈር ቀጥሎ የሚፈራው መጽሐፍ መደብር መዝለቅ ነው፡፡ ምናልባት መደብር ስንገባ ያላነበብናቸው መጻሕፍት አንድ ላይ ተሰብስበው ሲያፈጡብን ስለሚያስጨንቀን ይሆናል፡፡

በመጻሕፍትና በማያነብ ሕዝብ መሀል የረበበውን ይህንን ፍጥጫ አዝዋሪዎች ገብተው ያሸማግላሉ፡፡ መጀመርያ መጻሕፍቱን ያለንበት ድረስ አዝለው በማምጣት፣ ብሎም በተናጥል አገላብጠው እያስነኩ መጻሕፍቱ በፍጹም እንደማይናከሱ በማሳየት ያለማምዱናል፡፡

ሁለተኛ ስለ መጻሕፍቱ ይዘትና አስፈላጊነት ጭምር ይሰብኩናል፡፡ አናምን ስንላቸው ደግሞ የተወሰኑ ገጾችን እንዳነበቡ ጭምር ጥቅስ በመጥቀስ ልባችንን ያባቡታል፣ በፀፀት ይለበልቡናል፡፡ በመጨረሻም ሸክማቸውን ሳያወርዱ ጭምር ዘለግ ላለ ደቂቃ ከፊታችን ስለሚደነቀሩ በሐዘን አናታችንና ልባችንን ካረሰረሱ በኋላ ኪሳችንን ይተረትሩታል፡፡

ንባብ እስከዛሬ ሊቀጥል የቻለው በነዚህ መጽሐፍ በደረቴዎች ብርታት ብቻ ነው፡፡ እንጂ ይሄኔ መጻሕፍት እንደ ሕዝብ ስልክ ቅርስ ኾነው በቀሩ ነበር፡፡

***

ሳንሱርን ኢህአዴግ ገና ድሮ ቀዳዶ ጥሎታል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ፎቶ ኮፒ ማድረግ እንደማይከለከለው ሁሉ ያሻውን ጽፎ ማተም ይችላል፡፡ ቅድመ ኅትመት ሳንሱር ቢቀርም በድኅረ ኅትመት ሳንሱር መተካቱን ሳንዘነጋ፡፡ አንድ ደራሲ ብዕሩን ሲያነሳ በድኅረ ሳንሱር ሦስት ኃይሎችን ማሰብ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥትን፣ ብሔር ብሔረሰቦችንና አዝዋሪዎችን፡፡

መንግሥት የአንድ መጽሐፍ ይዘት ካላማረው ደራሲውን አንከብክቦ ያስራል፡፡ አልፎ አልፎ ነው ታዲያ፡፡ በዚህ ሊመሰገን ይገባል፡፡ የመለስና የኃይለማርያም መንግሥት ጋዜጣንና ጋዜጠኝነትን እንዳንገላቱት መጻሕፍትንና ደራሲያንን ያንገላቱ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት እየገዙት ያለው ሕዝብ መጻሕፍትን እምብዛምም የማያዘወትር በመሆኑ ተጽእኖው አልታይ ብሏቸው ሊሆን ይችላል፡፡

አምላክ ብሔር ብሔረሰቦችን ለምን ተቆጪ አድርጎ እንደፈጠረ አላውቅም፡፡ በረባ ባልረባ ቱግ ይላሉ፡፡ ክብራችን ተነካ፣ ተደፈርን፣ በማንወደው ስም ተጠራን፣ እያሉ በሆነ ባልሆነው ይቆጣሉ፡፡ ሲቆጡ ደግሞ አይጣል ነው፡፡ መጽሐፍ ሰብስበው ያቃጥላሉ፤ ደራሲውንም ቢያገኙት አመድ ከማድረግ አይመለሱም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ዋንኛ ችግር የግል ጭንቅላታቸውን ቆልፈውበት ሲያበቁ አንድ ጭንቅላትን በደቦ መጠቀም መምረጣቸው ነው፡፡ መጻሕፍት ደግሞ የግል ጭንቅላትን እንድንጠቀም ስለሚያበረታቱ በብሔረሰቦች አይወደዱም፡፡

ከመንግሥትና ከብሔር ብሔረሰቦች ቀጥሎ ሳንሱሮች አዝዋሪዎች ናቸው፡፡

መጽሐፍ በደረቴዎች ከመታወቂያቸው ጎን ሻጥ የሚያደርጓት ምላጭ እንዳለቻቸው አውርተናል፡፡ ምላጭዋ የዋጋ ተመን ማውጫ ናት፡፡ ደራሲ ማስፈራሪያም ጭምር ሆና ታገለግላለች፡፡ አንድ ደራሲ ለመጽሐፉ ዋጋ ሲተምን ለምላጭ ቆራጩ እንዲመች አድርጎ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የጀርባ ዋጋን በአሐዝ ቀርቶ በፊደል ያተመ ደራሲ ወዮለት፡፡ አዝዋሪዎች ጆሮውን ይቆርጡታል፡፡ ለምሳሌ ዋጋው 58 ብር የሆነ መጽሐፍ ከፊቱ ዜሮ ዜሮ ካልተጨመረ ለፍቀት ያስቸግራል፡፡ ዜሮ ዜሮ የሚጨመረው 58 ብርን ከፊት ያለችውን 5 ቁጥር ገድፎ ወደ 80 ብር ለማሳደግ ምቹ ስለሚሆን ነው፡፡ስለዚህ ደራሲው ምላጭ እያሰበ መጻፍ ይኖርበታል፡፡

ደራሲን ከአንባቢ የሚያገናኘው ድልድይ የተገነባው አዝዋሪዎች በሚያቀርቡት አሸዋና ሲሚንቶ ነው፡፡

የአዝዋሪዎች ምላጭ ስል ነው፡፡ በአንዳች ምክንያት የጎነተላቸውን ደራሲ ጣት ይቆርጣል፡፡ አንድ የማነቃቂያ መጽሐፍ በማተም የሚታወቅ ዶ/ር ደራሲ ራዲዮ ላይ ቀርቦ ይህን ስል የሆነ ምላጫቸውን በማጋለጡ ከዚያ በኋላ የጻፋቸው መጻሕፍት አውላላ ሜዳ ላይ ቀርተዋል፡፡ ለኪሳራም ተዳርጎ ነበር፡፡ ኋላ አማላጅ ወደ አዝዋሪዎች ልኮ ነው ከአንባቢዎቹ ጋ መገናኘት የቻለው፡፡

መጽሐፍ በደረቴዎች በብዛት ከአንድ አካባቢ መምጣታቸው ለብሔራቸው እና ብሔራቸው ለሚከተለው ሕብረብሔር ዘመም ፖለቲካ ታማኝና ጠበቃ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ህወሓታዊ መጻሕፍት ‹‹ነጃሳ›› ተደርገው ይታያሉ፡፡ አፍቃሪ መንግሥት ደራሲያን ደግሞ መስጊድ እንደገባ ውሻ ‹‹ቲሽ›› ይባላሉ፡፡ የነበረውን ሥርዓት ደግፎ የጻፈ ደራሲ እንደ ብቅል ሻጭ መጻሕፍቱን ራሱ ተሸክሞ ያዞራታል እንጂ አንድም አዝዋሪ አይተባበረውም፡፡ አቶ መለስን አንቆለጳጵሰው የጻፉ ደራሲዎች ለትእምት የስፖንሰር ጥያቄ የሚያቀርቡት ወደው አይደለም፡፡ አንድም ጥሩ ብር ፈልገው ነው፤ አንድም ሕዝብ ጋ ሊደርሱ የሚችሉበት ድልድይ እንደተሰበረ ስለሚያውቁ ነው፡፡

***

ያ የጓድ ኃይለማርያም ዘመን ለአታሚዎች ፈተናም በረከትም ነበረው፡፡ ኮስታራ ፖለቲካዊ መጻሕፍትን መንግሥት በከለከላቸው ቁጥር የሕዝብ የማንበብ ፍላጎት በዚያው መጠን ይንራል፡፡ ፍላጎት ሲንር ዋጋ ያሻቅባል፣ ዋጋ ሲያሻቅብ ትርፍ ይፋፋል፡፡ በዚህ የተነሳ አንዳንዴ አታሚዎች የዕውቅ ጸሐፊዎች በእስር መቆየት እንደ በረከተ-መርገምት ሳይመለከቱት ይቀራል? ለዚያም ይመስለኛል ቅዳሜና እሑድ ቃሊቲና ቂሊንጦን ያለወትሯቸው የሚያዘወትሩት የነበር፡፡ አንድም እውቅ ፖለቲከኛን ለመጠየቅ፣ አንድም ለማስፈረም፡፡

ማተሚያ ቤቶችም እንዲያ ነበሩ፡፡ የጠጣር ፖለቲከኞችን መጽሐፍ ለማተም የሚጠይቁት የዋጋ ተመን እንደ ቄሮ አመጽ ይፋጅ ነበር፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜማ የፖለቲካ መጽሐፍ ማሳተሚያ ዋጋ ሰማይ ነካ፡፡ በዚያን ወቅት የፕ/ር መስፍንን አንድ መጽሐፍ ማተም የምንሊክ ቤተ መንግሥት በር ላይ ቆሞ ‹‹መለስ ዜናዊ ኢዝ ኤ ዲክቴተር›› ብሎ ከመጮኽ እምብዛምም አይለይም ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ ኅቡዕ ማተሚያ ቤቶች ተወለዱ፡፡ በጠፍ ጨረቃ ማሽን የሚያንቀሳቅሱ ማተሚያ ቤቶች፡፡ ከጥበቃ እስከ ጠራዥ በታማኝ ዘመዶች ብቻ የሚሠራባቸው ቤቶች፡፡ ብቻ መንግሥት የጨለማ እስር ቤቶች እንደነበሩት ሁሉ ገናና ማተሚያ ቤቶችም በየሥርቻው ቅርንጫፍ የጨለማ ማተሚያ ቤቶችን ከፍተው ነበር፡፡

በዚያ የአስቸኳይ ጊዜ ዘመን እነዚህ የጨለማ ማባዣ ማሽኖች ገቢ ብራማ ሆነ፡፡ ለምን ግን እንዲህ ታደርጋላችሁ ሲባሉ "አሜሪካም በ2ኛው የዓለም ጦርነት የጦር መሣሪያ ንግድ ነው የበለጸገችው፡፡" ይሏችኋል፡፡ መቼም፣ ከመጻሕፍት ጋ እየተዳራ የሚያመሽ ሰው መልስ አያጣም ፡፡

Like what you read?

Take action for freedom of expression and donate to PEN/Opp. Our work depends upon funding and donors. Every contribution, big or small, is valuable for us.

Donate on Patreon
More ways to get involved

Search